በመድኃኒት አጠቃቀም ዙርያ የሚታዩ ስህተቶች


አዘጋጅ፡ ኃይለማርያም ሽመልስ 

የመድኃኒት መረጃ ማእከል ፋርማሲስት 

ውድ አንባብያን በአብዛኛው ታካሚዎች በመድኃኒት አጠቃቀም ዙርያ የሚታዩ ስህተቶች እና ስለመፍትሔዎቻቸው የሚያስረዳ አስተማሪ ጽሑፍ እነሆ፡፡ ጽሑፉን በማንበብ እና በማስነበብ የሕብረተሰባችንን በመድኃኒት ዙርያ ያለውን ንቃተ ሕሊና እንዲጎለብት ብሎም በመድኃኒት አጠቃቀም ዙርያ ለሚከሰቱት ችግሮች መረጃውን በማካፈል የበኩልዎትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እናሳስባለን፡፡

 1. እርስ በርስ የሚጋጩ መድኃኒት (ምግብና መጠጥ) አብሮ መውሰድ
  • አንዳንድ መድኃኒቶች እርስ በርሳቸው አሊያም ታካሚዎች ከሚበሏቸው ምግብና መጠጦች የሚጋጩ በመኖራቸው ከመውሰዳቸው በፊት ዶክቶር ወይም ፋርማሲስትን በጋራ ስለሚወስዷቸው መድኃኒቶችን መጠየቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ቴትራሳክሊን የተሰኘው መድኃኒት ሲወሰድ ወተት ቢጠጣ ወተቱ የመድሃኒቱን የማሻል አቅም በማደናቀፍ ኃይሉን ይቀንሰዋል፡፡
   1. መፍትሔ፡- አንዳንድ መድኃኒቶች እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ መድኃኒቶችን ከመውሰዳቸው በፊት ዶክቶር ወይም ፋርማሲስትን በጋራ ስለሚወስዷቸው መድኃኒቶችን መጠየቅ ይገባል፡፡ ስለአመጋገብ ሁኔታዎች ለምሳሌ ስለሚከለከሉ ወይም ከመድኃኒቱ ጋር አብረው መወሰድ ያለበት የአመጋገብ ስልት ታካሚዎች ባለሞያውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡

      

 1. ከምርመራ ክፍል ያለ በቂ (አነስተኛ) በመድኃኒት ዙርያ መረጃ ይዞ መውጣት
  • በብዙ ታካሚዎች ከሚታዩ ችግሮች መካካል አንዱ የሆነው የሕክምና አገልግሎት ከተረከቡበት የምርመራ ክፍል ሲወጡ ስለታዘዘላቸው መድኃኒት ምንም ዓይነት መረጃ አለመጠየቃቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ሊጠይቁ ከሚገባቸው መረጃዎች ቢያንስ የታዘዘው መድኃኒት ስም፣ የታዘዘበት ዓላማ የአወሳሰድ ሒደቱ ወዘተ. . . ተጠቃሽ ናቸው፡፡
   • መፍትሔ፡- ከሐኪም ምርመራ ከፍል ከመውጣትዎ በፊት ስለሚወስዱት መድኃኒት ስም፣ ለምን እንደታዘዘ እና እንዴት፣ በምን ያህል መጠን መወሰድ እንዳለበት ጠይቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የጽሑፍ ማብራሪያ መያዝ የመረጃ ክፍተትን ይሞላል፡፡ 

 1. መድኃኒቱ በታዘዘበት መንገድ አለመውሰድ
  • በሐኪም ታዝዞ በመድኃኒት ባለሞያ የተሰጠውን መድኃኒት በአግባቡ በታዘዘው መልኩ መድኃኒት አለመውሰድ ሌላኛው በታካሚዎች ላይ የሚታየው ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የእንክብል መድኃኒቶች በፈንጣጣ አሊያም በማሕፀን የሚወሰዱ መድኃኒቶችን በአፍ መዋጥ፣ ተበጥብጦ የሚጠጡ ፈሳሽ መድኃኒቶችን ሳይበጠብጡ መውሰድ፣ ወዘተ. . .
   • መፍትሔ፡- ከጤና ባለሞያ ስለመድኃኒቱ አወሳሰድ የሚሰጠውን ምክር በጥሞና ማድመጥና ግር ያለ ነገር ሲኖር ማብራሪያ መጠየቅ፡፡ በተጨማሪም ከፋርማሲ ሲወጡ በጽሑፍ የተደገፈ ማብራሪያ ስለአወሳሰዱ መቀበል ማረጋገጥ፡፡
 1. መድኃኒቱ በታዘዘበት ወቅትና መጠን አለመውሰድ
  • መድኃኒት የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ከሚያስፈልጉ ሁኔታዎች መካከል በአካላችን ውስጥ መድኃኒቱ በሚያስፈልግበት መጠን መገኘቱ ነው፡፡ ነገር ግን በታዘዘበት ወቅት እና መጠን መድኃኒት ባልተወሰደ ጊዜ በአካላችን ውስጥ የሚገኘው መጠን ሕመምን ለማከም ከሚጠበቀው በላይ ከፍ አሊያም ዝቅ ይላል፡፡
   • መፍትሔ፡- መድኃኒቱ በታዘዘበት ጊዜ ለመውሰድ እንዲረዳ ከመድኃኒት ባለሞያ መድኃኒቱን ለመውሰድ አመቺ ጊዜ መመካከር፡፡ ከዚህም ሌላ የመድኃኒቱ መወሰድ ካለበት መጠን በፍጹም ጨምሮ አሊያም ቀንሶ አለመውሰድ ይገባል፡፡
 1. መድኃኒቶችን በተገቢው ቦታ አለማስቀመጥ
  • መድኃኒቶች ጥራታቸው ጠብቀው እንዲቆዩ ተገቢ የአቀማመጥ ቦታ አላቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ መድሃኒቶች በማቀዝቀዣ ውስጥ መቀመጥ ሲኖርባቸው ሌሎች ደግሞ በከባቢ አየር ሙቀት ባላቸው ስፍራ በመቀመጥ አለባቸው፤ ሌሎች ከቀጥታ የፀሐይ ጨረር መጠበቅ ሲኖርባቸው ሌሎች ደግሞ ከእርጥበት መጠበቅ ለመድኃኒቱ ጥራትና ብቃት አለባቸውሕጻናት በማይደርሱበት ቦታ አለማስቀመጥ፡፡ ነገር ግን ታካሚዎች መድኃኒቶችን የት ማስቀመጥ እንዳለባቸው ባለመረዳታቸው ተገቢ ባልሆነ ቦታ ያስቀምጣሉ፡፡

 • መፍትሔ፡- የመድኃኒት ባለሞያውን እንዴት እና የት መድኃኒቱን ማስቀመጥ እንደሚገባ በመጠየቅ የሚሰጠውን ምክር በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ፡፡ የትኛውን መድኃኒት ሕጻናት በማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ፡፡
 1. በመጨረሻም የትኛውንም ዓይነት መድኃኒቶችን አብሮ ከአልኮል ጋር መውሰድ አይገባም

 

Advertisements

ዝንጅብልና ጠቀሜታዎቹ


አዘጋጅ፡ ኢልሃም ረሺድ


 

ዝንጅብል በተለምዶው ለቅመም የምንጠቀምበት ተክል ሲሆን ከዚህ ያለፈ ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት የተለያዩ መረጃዎች ይተነትናሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ በምግብና መጠጥ ፋብሪካዎች እንደ ማጣፈጫ እንዲሁም በሌሎች ሳሙና እና ኮስሜቲክ ፋብሪካዎች ደግሞ ለማራኪ መኣዛነት ይጠቀሙታል፡፡ ሌላኛውና ዋናው ጠቀሜታ ደግሞ ከጤና ጋር የተያያዘ ሲሆን በተለያዩ ለሆድ የሚዘጋጁ መድሃኒቶች ላይ ተካትቶ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ እትም ወይም ፅሁፍ ላይ በመረጃ ስለተረጋገጡ የዝንጅብል ጤናማ ሚናዎችን እንዳስሳለን፡፡

ዝንጅብል ከያዛቸው ንጥረ ነገሮች መካከል አንደኛው ጂንጀሮል ነው፡፡ ይሄም ንጥረ ነገር ዝንጅብል ለሆድ እና አንጀት ተያያዢ ችግሮች እንዲሁም ለተለያዩ ህመሞች እንድንጠቀመው አስፈላጊ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም ዝንጅብል ለሚከተሉት የጤና ችግሮች ልንጠቀመው እንደምንችል የተለያዩ መረጃዊ ዕሁፎች ያመለክታሉ፡፡

 • ለማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ችግሮች 

 እነዚህ ችግሮች የሆድ ህመም ሲኖር አልያም የተለያዩ የጤና እንከኖች ሲኖሩ እንደምልክት የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ. ዝንጅበል በያዘው ንጥረ ነገር አማካኝነት ሆድና አንጀት ላይ የሚገኙትን ጡንቻዎችን በማፍታታት ለቁርጠት ሁነኛ ፋታ ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሻይ መልክ (በውሃ ብቻ በማፍላት) በማዘጋጀት ወይም ጥሬውን ዝንጅብል በማኘክ (የጨጋራ ማቃጠል ህመም ከሌለ)ማቅለሽለሽ እና ማስታወክን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የማቅለሽለሽ ምልክትም እንድናክም ይጠቅማል፡፡

 • ለሪህ ህመም  

  ከላይ እንደተገለዐው ሌላኛው የዝንጅብል ጥቅም ከህመም ማሰታገሻነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዳሉት መረጃዎች ከሆነ ዝንጅብል በሪህ ጊዜ የሚከሰተውን የጉልበትና የጭን መገጣጠሚያ ህመሞችን በተወሰነ መልኩ የመቀነስ ባህሪይ አለው፡፡ እኛ ሀገር (ኢትዮጵያ) ውስጥ ባይገኝም በተለያዩ ሀገሮች ዝንጅብል በአፍ በሚወሰድ እንክብል መልኩ ይዘጋጃል፡፡ የተለየዩ መረጃዎች እንደሚያስቀምጡት ከሆነ አንድ 500 ሚ.ግ እንክብል በቀን ሁለት ጊዜ ሲወሰድ እንደሌሎች ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ተመሳሳይ ውጤት አሳይታል፡፡ ስለሆነም ህመም በሚሰማን ወቅት ዝንጅበልን አቅራቢያችን በሚገኘው መልኩ ማዘውተር ተመራጭ ነው፡፡

 • ለወር አበባ ህመም

የተወሰኑ ዕሁፋዊ መረጃዎች እንደሚተነትኑት ዝንጅብል በወር አበባ ጊዜ ሲወሰድ ተያይዘው የሚመጡ የህመም ምልክቶችን ይቀንሳል፡፡ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው አንድ 250 ሚ.ግ የዝንጅብል እንክብል በየቀኑ ለሦሥት ቀን በወሰዱ የጥናቱ 62 በመቶ ሰዎች ላይ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የነበረውን ህመም ቀንሷል፡፡ እዚህ ሀገር እንክብሉ ባይገኝም በገበያ ላይ ወይም ቤታችን ውስጥ የሚገኘውን ጥሬ ዝንጅብል ወይም በሻይ መልኩ የተዘጋጀውን መጠቀም እንችላለን፡፡

 

ከላይ ከተገለፀው ጠቀሜታዎች በተጨማሪ ዝንጅብል ለሌሎች ቀጥለው ለተዘረዘሩት የጤና ችግሮች መፍትሄ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህን በተመለከተ የተሰሩ መረጃዎች በቂና አጥጋቢ አይደሉም፡፡

 

 • ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ችግሮች
 • ለምግብ አለመፈጨት
 • በካንሰር ጊዜ ለሚከሰት የማቅለሽለሽ ስሜት
 • ለከፍተኛ ደም ውስጥ ቅባት ለመቀነስ
 • በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥመውን ምጥ ለማፋጠን
 • ለማይግሬን ራስ ምታት
 • ለመዋጥ ችግር
 • ለምግብ ፍላጎት መቀነስ እንዲሁም
 • ለጉንፋን

 

ነገር ግን ዝንጅብል ከጉዞ በፊት ለሚከሰት የማቅለሽለሽ ስሜት እና ለሰውነት ክብደት መቀነስ ምንም ጠቀሜታ የለውም፡፡

 

የዝንጅብል አወሳሰድ

በሻይ መልክ፡ ሁለት የሻይ ማንኪያ የተከተፈ ዝንጅብል በአንድ የሻይ ሲኒ ውሃ ለ ሃያ ደቂቃ ማፍላት እና መውሰድ ይቻላል፡፡ በጉንፋን ጊዜ፣ ሎሚና ማር ጨምረን ብንጠጣ የበለጠ ጠቀሜታ አለው፡፡

ዝንጅብሉን በመዘፍዘፍ፡  ሁለት የሻይ ማንኪያ ዝንጅብል በ አንድ ከግማሽ የሲኒ ውሃ በምዘፍዘፍ ለ አስር እስከ አስራ አምስት ደቂቃ ማቆየትና መጠጣት ይቻላል፡፡

 • ከነዚህም በተጨማሪ ጥሬውን ዝንጅብል በማኘክ ጠቀሜታውን ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

ምንጭ፡-

http://www.ncbi.nlm.nih.gov/books/NBK92775/

http://www.webmd.com/food-recipes/warm-up-to-ginger?page=2

http://www.mayoclinic.org/tests-procedures/chemotherapy/expert-answers/ginger-for-nausea/faq-20057891

https://umm.edu/health/medical/altmed/herb/ginger